ሐምሌ 9 ቀን 2018 ዓ.ም. (July 16, 2026) የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በአዲስ አበባ–አዳማ ፈጣን መንገድ ላይ በሚገኘው TAF ENERGIES Smart Station (ኪ.ሜ. 29) የሥራ ጉብኝትና የምክክር ፕሮግራም አካሂዷል። መርሃ ግብሩ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር፣ በጣቢያው የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለመገምገም እና ለወደፊቱ የጋራ የልማት አቅጣጫዎችን ለመወያየት የተዘጋጀ ነበር።
በፕሮግራሙ ላይ የታፍ ሆልዲንግ ከፍተኛኃላፊዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ተገኝተው በጣቢያው አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም፣ የተገልጋዮች አገልግሎት፣ የአሠራር ብቃት እና የወደፊት የልማት እቅዶች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል። ውይይቱ በተለይ በተገልጋዮች እርካታ፣ በአገልግሎት ጥራት፣ በኦፕሬሽናል ብቃት እና በቀጣይ የሚወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች ላይ ትኩረት አድርጓል።
በዚህ አጋጣሚ የታፍ ማኔጅመንት አባላት ለፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ሁሉ ከልብ የመነጨ ምስጋና አቅርበው፣ ለተቋማቱ የጋራ ስኬት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ አድንቀዋል። በተጨማሪም በጣቢያው የተስተዋሉ ክፍተቶችን በመለየት የማሻሻያ እቅዶችን በጋራ በመተግበር የተገልጋዮችን እርካታ እና የአገልግሎት ጥራት የበለጠ ለማሳደግ የሁሉም አካላት ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
TAF ENERGIES Smart Station (ኪ.ሜ. 29) በአዲስ አበባ–አዳማ ፈጣን መንገድ ላይ ለሚጓዙ ተሽከርካሪዎችና ተጓዦች ዘመናዊና የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል ሲሆን፣ የነዳጅ አገልግሎት፣ ምግብ ቤት፣ ካፌ፣ ሱፐርማርኬት እና ሌሎች የጉዞ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ በማቅረብ በኢትዮጵያ የመጓጓዣ ዘርፍ ውስጥ ጠቃሚ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በዚህ ምክክር የተደረጉ ውይይቶችም ይህንን አገልግሎት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ ጠንካራ መሠረት ፈጥረዋል።
የፕሮግራሙ ማጠቃለያ በልዩ የእውቅና ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል። በዚህም በየጊዜው በ ኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ለሚደረገው ድጋፍ በአቶ ናስር አማካኝነት ለተቋሙ የእውቅና ዋንጫ እና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል። ይህ እውቅና የጋራ ስኬትን የሚያበረታታ እና በቀጣይም የተሻለ የሥራ ትብብር እንዲኖር የሚያበረክት መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ እና TAF ENERGIES ወደፊትም በመተባበር የመንገድ አጠቃቀምን የበለጠ ለማዘመን፣ ለተጓዦች የተሻለ አገልግሎት ለማቅረብ እና ለኢትዮጵያ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት እድገት የሚያበረክቱ የጋራ ሥራዎችን በቀጣይነት እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።
